የክልሉ አስተዳደር ምክር ቤት 4 ረቂቅ አዋጆችን ለጨፌ ኦሮሚያ አቀረበ

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባ የክልሉን ሕዝብ የሰላምና የልማት ጥያቄዎች ለመመለስና የክልሉን የማስፈፀም አቅም ለማጎልበት ያስችላሉ ያላቸውን አራት ረቂቅ አዋጆችን በጨፌ ኦሮሚያ ለማስጸደቅ ማቅረቡን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ረቂቅ አዋጆቹን በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከረቂቅ አዋጆቹ አንዱ የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ ከገዳ ሥርዓት የተቀዳና በሕዝብ አደረጃጀት የአካባቢን ሰላም ማረጋገጥ የሚያስችል “ጋቸና ስርና” የተሰኘን አደራጃጀት ማቋቋም የተመለከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሌላው ረቂቅ አዋጅ እያጋጠመ ያለውን የተፈጥሮ አደጋ ለመቋቋም የሚያስችልና ከገዳ ሥርዓት የተቀዳ “ጋዲሳ ቡሳ ጎኖፋ” የተሰኘ የሕዝብ መረዳጃ ማቋቋም የተመለከተ መሆኑን አመልክተዋል።

“ጋዲሳ ቡሳ ጎኖፋ” አሁን ላይ በሥራ ላይ ያለውን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንን የሚተካ እንደሆነም አመላክተዋል።

የክልሉን የልማት ፍላጎትና የገበያ አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያስችል የመንግሥት የልማት ተቋማት አስተዳደር ማሻሻያም ሌላኛው ለጨፌው የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

ቀደም ሲል 10 ብቻ የነበሩት የክልሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብዛት አሁን ላይ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በክልሉ 27 መድረሳቸውን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ለሕዝብ አገልግሎት ለማዋልና በተፈጥሮ አደጋ የደረሱ ጉዳቶችን ለመቋቋም የሚያስችል የ13 ነጥብ 95 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅም በአስተዳደር ምክር ቤቱ ለጨፌው መቅረቡን አስታውቀዋል።

ረቂቅ አዋጆቹ በጨፌ ኦሮሚያ ውይይት ተደርጎባቸው ይጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የቢሮው ኃላፊ በመግለጫቸው መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።