የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በቡታጅራ ከተማ ተጀመረ

ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) – የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር “በወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሀሳብ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃግብር በደቡብ ክልል ቡታጅራ ከተማ አስጀምሯል፡፡

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃግብሩን የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ህይወት ኃይሉ በጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ተገኝተው ያስጀመሩ ሲሆን፣ በመርኃግብሩ ከ36 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግና 16 ሚሊየን ወጣቶችን ለማሳተፍ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከ10 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ስራዎችን በነፃ ለማከናወን መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እስቴር ከፍታው በክልሉ ችግኝ ተከላን ጨምሮ በ12 የአገልግሎት ዘርፎች የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ለመስራት ታቅዷል ብለዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ መሃመድ ጀማል በበኩላቸው፣ ወጣቱ ጉልበቱን በበጎ ተግባር ላይ እያዋለው እንደሚገኝ ገልጸው፣ ዛሬ የተጀመረውን የችግኝ ተከላ በማጠናከር ሌሎች ስራዎችን ለመስራት ዝግጅት መጨረሳቸውን በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።

የዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሶስት ወራት የሚቆይ ሲሆን፣ በመርኃግብሩ ችግኝ መትክል፣ ደም ልገሳ፣ የአረጋውያን ቤት ማደስና ሌሎችም ተጨማሪ ተግባራት ይከወናሉ ተብሏል፡፡

ከነዚህ ተግባራት ጎን ለጎን ንባብ ለሁሉም ይዳረስ ዘንድ መጽሐፍት የማሰባሰብ ሥራ እደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡

በዚህ ዓመት ከክረምቱ በተጨማሪ የበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰጡ ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን፣ ለአብነትም የኮቪድ-19ን በመከላከል፣ ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ፣ ደም መለገስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

(በተስፋዬ አባተ)