የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የልዩ ኃይልና ፀረ ሽብር ኃይሎችን አስመረቀ

ነሐሴ 7/2016 (አዲስ ዋልታ) በኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የልዩ ኃይልና የፀረ ሽብር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት “አዳኞቹ” በሚል መጠሪያ ያሰለጠናቸውን 12ኛ ዙር የልዩ ኃይልና የፀረ ሽብር ኃይሎችን አስመረቀ፡፡
በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።
ተመራቂዎቹ ከዕዙ የተለያዩ ክፍሎች በግዳጅ አፈፃፀማቸውና በዲሲፕሊናቸው የተመረጡና የተሰጠውን አስቸጋሪ ስልጠና በአጥጋቢ ሁኔታ ያጠናቀቁ ናቸው ተብሏል።
ተመራቂዎቹ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚሰጣቸውን ግዳጅ በተናጠልም ሆነ በቡድን ለመፈፀም የሚያስችላቸውን ስልጠና የወሰዱ መሆናቸውም ተገልጿል።
በዝግጅቱ ላይ በተመራቂ የልዩ ኃይልና የፀረ ሽብር አባላቱ የተለያዩ ወታደራዊ ትዕይንቶች ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የተመራው የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች በዕዙ የልዩ ኃይልና የፀረ ሽብር ማሰልጠኛ የአረንጓዴ አሻራቸውንም አኑረዋል።