የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የከተማዋ የጤና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገለጹ

ሚያዝያ 12/2013 (ዋልታ) – በድሬዳዋ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የከተማዋ የጤና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ለዋልታ ገልጸዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎቹ የቫይረሱን የስርጭት መጠን ለመቀነስ እና የጤና ባለሞያዎች መብቶችንም ለማስጠበቅ ማህበር አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመላው አለም ስርጭቱ እየተባባሰ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያም በተለያዩ ከተሞች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን ከእነዚህ ከተሞች መካከል ድሬዳዋ አንዷ ነች፡፡

ባለሞያዎቹ በድሬዳዋ ከተማ ያለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው ለስርጭቱ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት የከተማዋ ነዋሪዎች የአፍን አፍንጫ መሸፈኛ ማስኮችን በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ነው ብለዋል፡፡

አክለውም ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ነዋሪዎቹ በአግባቡ ቢተገብሩ የቫይረሱን ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሺኝን እና ሌሎችንም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ስርጭት ለመቆጣጠር የጤና ባለሞያዎች ማህበር አስፈላጊ ነው የሚሉት ባለሞያዎቹ እንደ ድሬድዋ ከተማ ማህበር ማቋቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡

ማህበሩ በዋናነት በድሬዳዋ ከተማ የተስፋፋውን የኮቪድ-19 ሰርጭት ለመከላከል በተለይም ህብረተሰቡን በቁርጠኝነት ለማገልገል ይሰራል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም መብቶችን ለማስጠበቅ እና ሀገር እንደ ኮቪድ-19 አይነት ወረርሺኝ ስጋቶች ላይ ስትወድቅ የጤና ባለሞያዎች በማህበር መንቀሳቀሳቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

(በሜሮን መስፍን)