የኮቪድ- 19 ስርጭትን ለመግታት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ማጠናከር አስፈላጊ ነው”- አቶ ደመቀ መኮንን

ግንቦት 06፣ 2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ንቅናቄ ሀገር አቀፍ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ እንደተናገሩት አሁን ያለውን የኮቪድ 19 ስርጭት ለመግታት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ ለሁለት ወራት የሚቆይና በርካታ ዝርዝር ተግባራትን ያካተተ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ምላሽን ማጠናከር የሚያስችል ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 በሚል ሀገር አቀፍ ንቅናቄ አስጀምረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከብሄራዊ የኮቪድ- 19 ግብረሃይል፣ ከክልል ርዕሰ መስተዳደሮች እና ከተለያዩ ሴክተር መስርያ ቤቶች የተገኙ የስራ ሃላፊዎች ጋር በበየነ መረብ ባደረጉት ውይይት አሁን ያለውን የኮቪድ -19 የስርጭት ሁኔታ እየተገበርነው ባለው የምላሽ አካሄድ መፍታት ስለማይቻል ምላሹን ከጤና ሴክተር ባለፈ ሁሉን አቀፍ ምላሽን ማጠናከር፣ የአመራርና የህብረተሰቡን ትኩረትና ተሳትፎ ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ወቅታዊውን አለም አቀፍና አገር አቀፍ የኮቪድ 19 ሁኔታን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በየደረጃዉ ያለው አመራርና የሚመለከተው አካላት ሁሉ ለንቅናቄው ስኬት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በቅንጅት ህብረተሰቡን በማሳተፍ መስራት ይጠበቅበታልም ብለዋል አቶ ደመቀ ፡፡
ሚኒስትሩ የሚዲያ አካላትና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች፣ ከኪነጥበብ ባለሙያዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ህብረተሰቡን ማንቃትና ቫይረሱ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ማሳወቅ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸው፣ በመመሪያ ቁጥር 30 የተቀመጡ ክልከላዎችን ተከታትሎ ማስፈጸምና የተቀመጡ ስታንዳርዶችን ሳያሟሉ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ላይ አስፈላጊዉ እርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለሁለት ወራት የሚቆየውን ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ዝርዝር እቅድ ያቀረቡ ሲሆን፣ አሁን ላይ ያለው የቫይረሱ ስርጭት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው፣ የኮቪድ- 19 ስርጭት መቀልበስና የሞት መጠንን መቀነስ ፣ የዘርፈ ብዙ ምላሽን ማጠናከር፣ የኮቪድ-19 ጽኑ ህክምና ተደራሽነት ማሳደግ፣ የተቀናጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የህግ ማስከበር ንቅናቄዎችን ማከናወን፣ የምርመራ ዓቅምና የክትባት ሽፋንን ማሳደግ ላይ ትኩረት በመስጠት ይሰራል ነው ያሉት ፡፡
በንቅናቄውም የቤት ለቤት ዳሰሳ ስራ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አጠቃቀም ተግባራዊ ማድረግ፣ አካላዊ ርቀት አተገባበርን መከታተል፣ እለታዊ አማካይ የመመርመር አቅምን ከፍ ማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት ዶ/ር ሊያ፣ የሁለት ወር ንቅናቄው ውጤት ተገምግሞ አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ ምላሹ የሚቀጥል ይሆናል ማለታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡