የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት የሚዲያ ዘርፉ ትልቅ ተጋድሎ ማድረጉ ተገለጸ

ነሐሴ 26/2013 (ዋልታ) – የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት የሚዲያና የተግባቦት ዘርፉ ትልቅ ተጋድሎ ማድረጉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ፡፡

ሚኒስትሯ ከኮቪድ መከሰት በኋላ ሁሉም የሚዲያና የተግባቦት አውታሮች መሉ ጊዜያቸውን ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ መረጃዎችን በመስጠትና የተግባቦት ስራ በመስራታቸው የጉዳቱን መጠን መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡

ለዚህ ስራ መሳካት ርብርብ ላደረጉ አካላትም ሚኒስትሯ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ከድንገተኛ ወረርሽኞች በተጓዳኝ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሚዲያዎች የንቃተ-ጤና ትምህርት ከመስጠት አንፃር ትልቅ ሚና ያላቸው በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት፡፡

የሲዲማ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው፣ ባለፈው አንድ አመት የጤናው ዘርፍ አስቸጋሪ ተግዳሮት ገጥሞት እንደነበር በማንሳት በተደረገው የጋራ ጥረት አበረታች ለውጥ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡

ለተገኘው ውጤት የሚዲያና የተግባባት ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ በበኩላቸው፣ የተግባቦቱ ዘርፍ ኮቪድ-19ን የተመለከቱ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ ረገድ ገንቢ ውጤት ማስመዝገቡን አንስተው በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት ሊቀረፍ ይገባል ብለዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት አመት አመርቂ ስኬት በተግባቦት ዘርፍ ላስመዘገቡ የክልል የጤና ቢሮዎችና ባለድርሻ አካላት የዕውቅና ስነ-ስርዓት የተካሄደ ሲሆን፣ በመድረኩ የ2013 ዕቅድ አፈጻጸምና የ2014 ዕቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የተገኘው ዘገባ ያመላክታል፡፡