የወሎ፣ መቅደላ አምባና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር ዳግም ሥራ እንደሚጀምሩ ተገለፀ

ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)

ጥር 27/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው ሕወሓት ዘረፋና ውድመት የተፈፀመባቸው የወሎ፣ መቅደላ አምባ እና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ተማሪዎችን በመቀበል ዳግም ሥራ የሚጀምሩ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንደገለጹት በአማራ ክልል አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ጦርነት ሳቢያ የወሎ፣ መቅደላ አምባ እና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ስራ አቋርጠዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው ወራት ዩኒቨርሲቲዎቹን ዘርፎና አውድሞ መሄዱን አስታውሰው በዳግም ጥገና ሥራ እንዲጀምሩ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

በመንግሥት ድጋፍና ባላቸው አቅም አስፈላጊ ግዥዎችንና ጥገናዎችን እንዲያካሂዱ ከማድረግ ባለፈ አማራጭ የትምህርት ማስኬጃ መንገዶችንም እንዲያስቡና ወደ ሥራ እንዲገቡ አሁንም ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ተማሪዎችን በመቀበል ዳግም ሥራ የሚጀምሩ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ የመጨረሻ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎችን ቀድመው በመቀበል ሌሎችንም በሚያወጡት መርሃ ግብር መሰረት የሚቀበሉ ይሆናል ተብሏል።

በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ተዛብቶ የቆየው የአካዳሚክ ካሌንደር በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ይስተካከላል ብለዋል።

የአካዳሚክ ካላንደሩን በማስተካከል በዩኒቨርሲቲዎች የተሳካ የመማር ማስተማር ሂደት እውን ለማድረግ አጠቃላይ የትምህርት ማኅበረሰቡ፣ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ሌሎችም የድርሻቸውን እንዲወጡ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://www.facebook.com/waltainfo

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!