ነሃሴ 4/2013(ዋልታ) – “ሁሉም ሰው የሚታወቅባት ኢትዮጵያን እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ የተጀመረው የወሳኝ ኩነት ቀን ለአራተኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።
የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ጃንጥራር አባይ እና ባለድርሻ አካላት ተገኘተዋል።
በ1935 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ የወሳኝ ኩነት የተጀመረ ሲሆን አገልግሎቱ ለውጭ ሃገር ዜጎች ብቻ የተገደበ ነበር። ባለፋት አራት አመታት ግን የህግ ማዕቀፋን በማሻሻል ስደተኞችን ጨምሮ ሁሉም ሰው አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረጉ ተገልጿል።
ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍቺ መመዝገቡ ለአንዲት ሃገር እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገልጿል።
የወሳኝ ኩነቶች መመዝገባቸው የዜጎችን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል የተገለፀ ሲሆን በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ይረዳል ያሉት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ጃንጥራር አባይ ናቸው ።
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በሚፈለገው መልኩ ውጤት እንዲያመጣ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠርና ወቅቱ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ መጠቀም የግድ እንደሆነ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ሙጂብ ጀማል ገልፀዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ሚኒስቴር በበኩላቸው መስሪያቤቱ ከኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ጋር በመተባባር የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጥሩ ውጤት ማምጣቱን ገልፀዋል። ባለፉት 12 ዓመታት ተግባራዊ እንዲደረግ ቢሰራም ሳይሳካ መቅረቱን የገለፁት ሚኒስትሯ ባለፋት ሁለት ዓመታት ግን ቴክኖሎጂውን በማዘመን ጥሩ ውጤት መገኘቱን በመግለፅ በአዲስአበባ የተጀመረው ይህ ጅማሬው በክልሎች እንዲካሄድ መስራት ያስፈልገናል ብለዋል።
(ነጻነት ጸጋይ)