የወባ በሽታን ለማጥፋት የ9.5 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ሚያዚያ 21/2014 (ዋልታ) የወባ በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል፡፡

የወባ በሽታን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የጤና ሚኒስቴርና የአሜሪካ ህዝብ ተራዓዶ ድርጅት USAID ናቸው ፕሮጀክቱን ይፋ ያደረጉት።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ፕሮጀክቱ በ8 ክልሎች በሚገኙ 54 ወረዳዎች ላይ የወባ ቅኝት ለማድረግና ለማጥፋት ተግባራዊ የሚደረግ ነው ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር በአጠቃላይ በ565 ወረዳዎች ላይ ወባን ለማጥፋት እየሰራ መሆኑንም ሚኒስቴር ዴኤታው ገልፀዋል።

የአርማወር ሀንሰን የምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አፍወርቅ ካሱ (ፕ/ር) ሁሉም ስለ ወባ በሽታ ሊነጋገር ይገባል ያሉ ሲሆን  ከምርምር ማዕከላት የሚወጡ የጥናት ውጤቶችን ወደተግባር በመቀየር የወባ በሽታን ማጥፋት ይገባናል ሲሉ ነው የገለፁት።

በኢትዮጵያ USAID ዳይሬክተር ሴአን ጆንስ እንደ ፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር ከ2007 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወባን ለማጥፋት 480 ሚሊዮን ዶላር ወጭ አድርገናል ብለው፤ አሁኑም ለአምስት አመታት የሚቆይ የ9 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አድሮገናል። ኢትዮጵያ የወባ በሽታን በማጥፋት ምሳሌ የሚሆን ተግባር ፈፅማለች ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በወባ በሽታ የሞት ምጣኔን 90 በመቶ በመቀነስ ውጤታማ ናት ብለዋል።

ዛሬ ለምረቃ የበቃው የአዳማ የወባ ስልጠና ማዕከል፤ በኢትዮጵያ በ1958 ዓ.ም 3 ሚሊየን ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውና 150 ሺህ ህዝብ መሞቱን ተከትሎ ናዝሬት የወባ መከላከልና ምርምር ማዕከል በሚል ስያሜ በ1959 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በወቅቱ 11ኛና 12ኛ ክፍል የጨረሱ ተማሪዎች በመመልመል ሲሰራ ነበር ተብሏል።

ማዕከሉ በ1993 ዓ.ም ቢ ፒ አር ተብሎ በክልል እንዲተዳደር የተደረገ ሲሆን ከ7 ዓመት ወዲህ ግን በጤና ሚኒስቴር ውስጥ በማድረግ በ60 ሚሊየን ብር ወጪ የማሻሻያ ግንባታው እንደተጀመረ ነው የተነገረው።

ማዕከሉ ባለ 9 ወለል ሲሆን ወባን ለማጥፋት ከሚያደርገው የምርምርና የመከላከል ስራ በተጨማሪ የቆላ በሽታ ላይም የምርምር ተግባራትን እንደሚያከናውን ተገልጿል።

በምንይሉ ደስይበለው