የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀረር በይፋ ተጀመረ

ሰኔ 22/2014 (ዋልታ) የ2014 ዓ.ም ሀገር ዐቀፍ የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በሀረር ከተማ በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተደድር ኦርዲን በድሪ በወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚከናወኑ ሥራዎች የማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በንቃት እንዲሳተፉ በተለይም ሰላምን ከማረጋገጥ አንፃር ሚናቸውን እንዲያጎለብቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በ2013 ዓ.ም 21 ሚሊየን ወጣቶችን ባሳተፈ መልኩ በተከናወነው የክረምት በጎ ፈቃድ እና የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት 38 ሚሊየን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም 10 ቢሊየን ብር ገንዘብ ማዳን መቻሉን ጠቁመው በዘንድሮው ዓመትም 19 ሚሊየን ወጣቶችን በማሳተፍ 40 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

የሚካሄደው ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ከወጣቶች ባለፈ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ በ7 ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች እንደሚከናወን አብራርተዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ መፍቱሃ አሊዪ በበኩላቸው የዘንድሮ የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በእለቱ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ ወጣቶችና የከተማ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ የችግኝ ተከላ እና የቤት እድሳት የማስጀመር መርኃ ግብር ተካሂዷል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)