የወጪ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስወገድ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

ታኅሣሥ 27/2015 (ዋልታ) የወጪ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩትን ችግሮች በመፍታት ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ የወጪ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት አልግሎት አሰጣጥ ላይ በተመዘገቡ ውጤቶችና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በመድረኩ ላይ በኮሚሽኑ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አዘዘው ጫኔ መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የወጪ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸው ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች መሠራታቸውን አመላክተዋል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሀገሪቱ የሚገባትን ገቢ እንድታገኝ ከጥገናዊ ለውጥ ባሻገር መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በመንግስት ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ጠንካራ መሆን እንዳለበት ያወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ ከወቅቱ ጋር የማይሄዱ የህግ ማእቀፎች እንደሚሻሻሉም ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ ዓለማውም የወጪ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት ዋና ዓላማ የኢኮኖሚ ልማትን ለማፋጠን፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማጎልበት፣ የካፒታል ፍሰትን ለማሳደግ ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እና ሀገራዊ ምርቶችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ መሆኑ ተመላክቷል።

የወጪ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት አዋጅ እና መመሪያ ወቅቱን የዋጁ አለመሆናቸውንና ሥርዓቱ ቀላል፣ ግልጽ እና ለቁጥጥር ምቹ አለመሆኑ ችግር ማስከተሉ በአስተያየት ተነስቷል።