የዋልታ ሰራተኞች የመጻሕፍት ማሰባሰብ መርኃ ግብር ጀመሩ

ሚያዝያ 22/2014 (ዋልታ) የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ሰራተኞች የአብርኆት ቤተ መጻሕፍትን ለመሙላት ለአንድ ወር በሚቆየው የመጽሐፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር መሰረት ማሰባሰብ ጀመሩ።

ለንባብ ባህል መጎልበት የንባብ ማዕከላት መስፋፋት ከፍተኛ ሚና ያለቸው ሲሆን ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ ለተገነባው የአብርኆት ቤተ-መጽሐፍ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የአንድ ሚሊዮን የመጻሕፍት ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ሀገር የሚገነባ አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር መጻሕፍትን ማሰባሰብና በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ማስቀመጥ ሁነኛ መፍትሄ ነው ሲሉ የአብርኆት ቤተ መጽሐፍን ለመሙላት በሚደረገው የመጻሕፍት ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር መሰረት ማሰባሰብ የጀመሩ የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ሰራተኞች ገልጸዋል፡፡

ማኅበረሰቡ በየቤቱ የሚገኙ መጻሕፍትን በማሰባሰብ እና በቤተ መጽሐፉ በማስቀመጥ የንባብ ባህሉ የበለጸገ፣ በስሜት የማይነዳ አስተዋይ ትውልድን የመፍጠር ኃላፊነት እንዳለበትም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ጥናትና ምርምር ለማድረግም ጭምር በተለይ ደግሞ አንዳንድ መጻሕፍትን ገበያ ላይ ፈልጎ ማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ ችግር ፈች በሚሆነውና እስከ አራት ሚሊዮን መጽሐፍት የመያዝ አቅም ባለው በአብርኆት ቤተ መጽሐፍ ውስጥ አሰባስቦ ማስቀመጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በአገር ዐቀፍ ደረጃ በንባብ ባህል የተቃኘ ትውልድ መፍጠር የሀገር ግንባታ አንደኛው መሰረት በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በማሰባሰቡ መርኃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን  ጥሪ አቅርበዋል፡፡