የዋይት ሃውስ አባላት ኮሮናቫይረስ ክትባቱን ቀድመው ሊወስዱ ነው

በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ባለስልጣናት የሆኑ የዋይት ሃውስ አባላት የኮሮና ቫይረስ ክትባቱን ቀድመው ከሚወሰዱት አሜሪካውን መካከል እንደሚሆኑ ተገለጸ።

አሜሪካ የፋይዘር/ባዮንቴክ ሰራሹን የኮቪድ-19 ክትባቶቹን “ወደ ሁሉም ግዛቶቿ” ማከፋፈል መጀመሯ ተገልጿል።

አሜሪካ ዜጎቿን ዛሬ መከተብ የምትጀምር ሲሆን፣ እስከ መጋቢት ማገባደጃ ድርስ 100 ሚሊየን ሰዎችን ለመከተብ ታቅዷል ተብሏል።

ክትባቱን ቅድሚያ የሚያገኙት ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ የሆኑት የጤና ባለሙያዎችና በእንክክብካቤ ማዕከላት የሚገኙ አረጋውያን መሆናቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ አሜሪካ መገናኛ ብዙሃን የዋይት ሃውስ ባለስልጣናትን ጠቀሰው እንደዘገቡት የዋይት ሃውስ አባላት ክትባቱን ቀድመው ከሚወስዱ አሜሪካውያን ተርታ ተሰልፈዋል።

አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ የዋይት ሃውስ አባላት ክትባቱን ቀድመው ማግኘታቸው የመንግሥት ሥራዎች ሳይቋረጡ እንዲከናወኑ ይረዳል።

በመጀመሪያው ዙር ክትባቱን የማከፋፈል ሥራ ለ3 ሚሊየን ዜጎቿ የሚሆን ክትባቶች በመላው የአሜሪካ ግዛቶች እየደረሰ ነው። የክትባት ስርጭቱን በበላይነት የሚቆጣጠሩት የአሜሪካ ጦር ጀነራል ጉስታፍ ፔርና ዛሬ ክትባቱ በአሜሪካ 145 ቦታዎች ይላካል ብለዋል። ነገ እና ከነገ በስቲያ ደግሞ ክትባቱ ወደ ተጨማሪ 491 ቦታዎች እንደምላክ ገልጸዋል፡፡

አሜሪካ ፋይዘር/ባዮንቴክ ያበለጸጉትን የኮሮናቫይረስ ክትባት ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲውል ፍቃድ መስጠቷ ይታወሳል።

ይህ ክትባት የኮሮናቫይረስ በሽታን በመከላከል 95 በመቶ አስተማማኝ መሆኑ ተገልጿል። ይኸው ተመሳሳይ ክትባት በዩኬ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረ ሲሆን በካናዳ፣ ባህሬንና ሳዑዲ አረቢያም ፈቃድ አግኝቷል ነው የተባለው።

በኮሮናቫይረስ ክፉኛ እየተጠቃች በምትገኘው አሜሪካ ከትናንት በስቲያ ብቻ 3 ሺህ 309 ዜጎቿን አጥታለች።

አኃዙን ሪፖርት ያደረገው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ድረገፅ የበለጠ እንደሚያስረዳው በአለም ላይ ከፍተኛ በቀን የተመዘገበ ሞትም አድርጎታል።

የፋይዘር/ባዮንቴክ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለአስቸኳይ ጊዜ መጠቀም ፍቃድ እንዲያገኝ በከፍተኛ ሁኔታ በትራምፕ አስተዳደር ጫና የተደረገበት የምግብና መድኃኒት አስተዳደርም ውሳኔውን የወረርሽኙ “አዲስ ምዕራፍ” ብለውታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡