የውጭ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነት እንደሚቃወም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ

ሀጂ መስኡድ አደም

ግንቦት 16/2013 (ዋልታ) – ለግድቡ ግንባታ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው በመቀጠል የውጭ ኃይሎች ግንባታውን ለማስተጓጎል የሚያደርጉትን ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴና ጣልቃ ገብነት እንደሚቃወም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ፡፡

የጉባኤው ምክትል ዋና ፀሀፊ ሀጂ መስኡድ አደም እንደገለጹት፤ የውጭ ኃይሎች የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመመከት ሕዝቡ አንድነቱን ማጠናከር ይኖርበታል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብን ግንባታ በተያዘለት እቅድ መሰረት እንዲካሄድ የሃይማኖት ተቋማት አማኞቻቸውን አስተባብረው መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ሀጂ መስኡድ፣ የውጭ ኃይሎች ግንባታውን ለማስተጓጎል የሚያደርጉትን ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴ ጉባኤው እንደሚቃወም አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ሂደትና የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትን የሚቃወሙበት ወሳኝ ወቅት መሆኑን የተናገሩት ሀጂ መስኡድ፣ ለግድቡ ግንባታ የቦንድ ግዢ በመፈጸምና በ8100 አጭር መልእክት ገንዘብ በመለገስ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዜጎች መካከል የሚስተዋለው የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት የሀገርን አንድነት ሊፈታተን እንደማይገባው ያመለከቱት ሀጂ መስኡድ፣ የውስጥ አለመግባባት ለውጭ ጥቃት አሳልፎ ሊሰጠን አይገባም ብለዋል፡፡

የሀገርን ጉዳይ በማስቀደም ለሉአላዊነት ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ሌላውን ጉዳይ ቀስ በቀስ መፍታት ይገባልም ብለዋል፡፡ ግብፅ የህዳሴው ግድብ ግንባታን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ለማስተጓጎል የውጭ ሃይሎችን አስተባብራ ዘመቻ ስትከፍት ኢትዮጵያውያንም አንድነታቸውን በማጠናከር መመከት እንደሚኖርባቸው ማሳሰባቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡