የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ

አምባሳደር መለስ አለም

ጥር 5/2015 (ዋልታ) የፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ፍሬያማና ተጨባጭ የሆነ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ አለም ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ጉዞ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ቻይና ከፊል የእዳ ስረዛ ማድረጓን ጠቁመው የሁለቱ አገራት ጠንካራ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የጀርመንና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ያለውን ሂደት ለመመልከት ብሎም አጋርነታቸውን ለማሳየት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

ሁለቱ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ከ125 ዓመታት በላይ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደር መለስ የሁለቱ አገራት ሚኒስትሮች ጉብኝነት ከፈረንሳይና ጀርመን ጋር አዲስ ምዕራፍ የፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በዛሬው እለት የሰባት አገራት አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን አስገብተው ተቀባይነት ማግኘቱን የገለጹት ቃል አቀባዩ አምባሳደሮቹ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ፋይዳው የጎላ እንደሆነ መናገራቸውን አንስተዋል፡፡

ሹመታቸው ተቀባይነት ካገኙ አገራት አምባሳደሮች መካከል የአልጀሪያ፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳው፣ እንግሊዝ፣ ሮማኒያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ይገኙበታል ተብሏል።

በሱራፌል መንግስቴ