የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ የ300 ሚሊዮን ዶላር አጸደቀ

ሚያዝያ 5/2014 (ዋልታ) ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ በዓለም ዐቀፍ ልማት ማኅበር በኩል የ300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮጀክት አጸደቀ፡፡

ፕሮጀክቱ የኅብረተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለመቅረፍ፣ በግጭት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም እና የግጭት ተፅዕኖዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡

መሰረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መሠረተ ልማትን መልሶ ለመገንባት ጥረት የሚያደረግ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በግጭት የተጎዱ ማህበረሰቦችን በተለይ በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ እና በንፅህና ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በፍጥነት ለመቅረፍ በፕሮጀክቱ በትኩረት እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡

በግጭቱ ምክንያት የስነ ልቡና ችግር የገጠማቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን የተሻለ አገልግሎት እና  እንክብካቤ እንዲያገኙ ይደረጋልም ተብሏል፡፡.

ፕሮጀክቱ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የድጋፍና የአገልግሎት ውስንነትን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኦስማን ዳዮኔ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በአፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች የሚተገበር መሆኑን  ከዓለም ባንክ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡