የዓለም የአዕምሮ እድገት ውስንነት ቀን በዲቦራ ፋውንዴሽን እየተከበረ ነው

መጋቢት 11/2014 (ዋልታ) “አካታችነት ስጦታ ሳይሆን ግዴታ ነው፣ አካታች ሥርዓትን መዘርጋት ብሎም ተጠቃሚ ማድረግ የዜጋ መብት ነው” በሚል የዓለም የአዕምሮ እድገት ውስንነት ቀን በዲቦራ ፋውንዴሽን እየተከበረ ነው፡፡
አካታችነትን ደጋግመን ብንናገረውም ተግባር ላይ ጉልህ ድርሻ ሲኖረው አይታይም የሚሉት የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራች አባዱላ ገመዳ ትኩረት ባለመስጠት፣ በፋይናንስ እጥረት እና በመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት ሳቢያ ለአካታችነት የተስተካከለ ምቹ ሥርዓት አለመኖሩን ገልፀዋል።
ይህንንም ለመቅረፍ በተለያዩ ዘርፎች እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው የመንግሥትና የግል የትምህርት ተቋማት አካታች ሆነው እንዲቀጥሉ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኃላፊነት መወጣት እችላለው በሚል በዲቦራ ፋውንዴሽን የተዘጋጀው መድረክ አካታች በማድረግ የነገ ተስፋ ያላቸውን ህፃናት ከተረጂነት ወደ ረጂነት መቀየር እንደሚቻል ተጠቅሷል።
የዓለም የአዕምሮ እድገት ውስንነት ቀንን በማስመልከት በዲቦራ ፋውንዴሽን እየተከበረ የሚገኘውን ቀን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በቂ ድጋፍና ክትትል ከተደረገላቸው አምራችና ብቁ ዜጋ መሆን እንደሚችሉ ገልፀዋል።
በሀኒ አበበ