የዓለም የጤና ድርጅትን ለአሸባሪው ሕወሓት መሳሪያነት መጠቀም ወንጀል ነው- ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ

ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) የዓለም የጤና ድርጅትን ለአሸባሪው ሕወሓት የፕሮፖጋንዳ መሳሪያነት መጠቀም ወንጀል ነው ስትል ታዋቂዋ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ለድርጅቱ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጋቢ ስተርን በጻፈችው ደብዳቤ ገለጸች።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ግንባር ቀደም አመራር ከሆኑ ግለሰቦች መካከል አንዱ እንደሆኑ በመጥቀስ አሸባሪው ሕወሓት በብርሃን ነጻ አውጪ በመምሰል፤ በጨለማ የሚገድል በጭካኔ የተሞላ ኢትዮጵያዊው ፋሽት ነው ብላለች።

አሸባሪው ሕወሓት ጊዜው እንዳበቃ መላ የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች መስክረዋል ያለችው ሄርሜላ የዓለም ጤና ድርጅት የቂም ዘር በአፍሪካ ምድር በመዝራት በሕዝቦች መካከል ጉድጓድ እየቆፈረ ነው ሰትልም አመልክታለች።

የትግራይ ሕዝብ በአሸባሪው ሕወሓት አመራር እና በጤና ድርጅቱ ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ምክንያት መከራን እያሳለፉ ይገኛሉ ስትል የገለጸችው ጋዜጠኛዋ አሸባሪው ሕወሓት ሚሊዮኖችን ያለፍላጎታቸው ለመግዛት የትግራይ ሕዝብን እንደ ማሲያዣነት እየተጠቀመበት ይገናል ብላለች።

ከባለፈው የሚያዝያ ወር ጀምሮ አስፈላጊ የሆነ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ቢያስታውቅም ዘ ጋርድያን ጋዜጣ በክልሉ ባለው ረሃብ ምክንያት ሴቶች እና ልጃገረዶች የአስገድዶ መደፈር ወንጀል እየተፈጸመባቸው እንደሚገኙ አስታውቋል።

ወደ ትግራይ የሚሄደውን እርዳታ ማን እየተጠቀመበት እንደሚገኝ የምትጠይቀው ሄርሜላ “እርዳታውን የተጠቀመበት ማነው የአሸባሪው ሕወሓት አባላት፣ የትግራይ ሕዝብ ወይስ በትግራይ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የተረድኦ ድርጅቶች አባላት” ስትል ትጠይቃለች።

እንደ ዓለም የጤና ድርጅት በሕዝብ ዘንድ የቀረችውን እንጥፍጣፊ ተአማኒነት ወደ ጎን በመተው አሸባሪው ሕወሓትን መደገፍ በትውልዶች ዘንድ ለዘመናት የማይረሳ ግፍ ነው ማለቷን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ድርጅቱ አፍሪካዊያን የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ መመለስ ባይችልም ብዙዎች በማኅበራዊ የመገናኛ መንገዶች እየተናገሩ ይገኛሉ ያለችው ሄርሜላ ለድርጅቱ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ያስገባቸው ድብዳቤ ማህደር የሚቀመጥ እና የድርጅቱን አጸያፊ ፕሮፖጋንዳ የሚያጋልጥ ነው ብላለች።

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!