የዓባይን ውሃ የተፋሰሱ አገራት ፍትሐዊነት ለመጠቀም ሊተባበሩና የጋራ ተጠቃሚነትን ሊያሰፍኑ ይገባል – ኡጋንዳዊ ፕ/ር

መስከረም 5/2015 (ዋልታ) የዓባይን ውሃ የተፋሰሱ አገራት በምክንያታዊና ፍትሐዊነት ለመጠቀም ሊተባበሩና የጋራ ተጠቃሚነትን ሊያሰፍኑ ይገባል ሲሉ የኡጋንዳ መከረሬ ዩኒቨርሲቲ ካሳጃ ፍሊፕ (ፕ/ር) ገለጹ።

በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም የፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቅም መርሕ መገለጫ ነው ብለዋል።

ዶክተር ካሳጃ ፍሊፕ በኡጋንዳው የመከረሬ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ህዝብ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር ናቸው።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገኘት የመጎብኘት አድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው ከነበራቸው ግምት በላይ የገዘፈና አህጉራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት መሆኑን አረጋግጫለሁ ብለዋል።

“ህዝብን በማስተባበር እንዲህ አይነት ፕሮጀክት መገንባት አስደናቂ ነው” ያሉት ፕሮፌሰር ካሳጃ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ የቀጣናውን የልማት ትሰስር በማጠናከር በኩል የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያና ኡጋንዳን ጨምሮ ለአካባቢው አገራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አሳላጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የጥቁር ዓባይ መነሻ እንደሆነች ሁሉ ኡጋንዳም የነጭ ዓባይ መነሻ በመሆኗ በፍትሐዊ የውሐ አጠቃቀምና የጋራ ጠቀሜታ ያላቸውን ፕሮጀክቶች እውን በማድረግ አርአያነት ያለው ተግባር እየፈፀሙ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓባይ ወንዝ ድንበር ተሻጋሪ ከሆኑ የአገራት የጋራ ሀብቶች አንዱ በመሆኑ፣ ምክንያታዊና ፍትሃዊ  የውሃ ሀብት አጠቃቅም ስርዓትን ማስፈን ተገቢ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቅም መርህ መገለጫ ፕሮጀክት እንደሆነ ተናግረዋል።

የዓባይ ውሃ ሃይል እያመነጨ ፍሰቱ ሳይገታ ተፈጥሯዊ ሂደቱን ጠብቆ እየተጓዘ መሆኑን በጉብኝታችን አረጋግጠናል የሚሉት ፕሮፌሰሩ የናይል ወንዝ ፍሰትን በተሳሳተ መልኩ የሚገለጹ መረጃዎች ፍፁም ከእውነታው ያፈነገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ጉዳይ ላይ የሚነሱ የድርድር ጉዳዮች የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ የመፍታት ማዕቀፍ እልባት ሊበጅላቸው እንደሚገባ ገልፀው ግድቡን ፖለቲካዊ መልክ መስጠት ተገቢ አይደለም ብለዋል።

በመሆኑም በግድቡ ላይ የሚነሱ ጉዳዮች ካሉ ከምዕራባዊያን መፍትሄ ይመጣል ብሎ ከመጠበቅ ይልቅ እንደ አፍሪካ በውይይት መፍታት ይቻላል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የውሃና መስኖ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ሮበርት አሚኖ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግሩም ምህንድስና ውጤት እንደሆነ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያዊያን የግድቡን ፕሮጀክት የመሩበትና የገነቡበት መንገድ ለሌሎች አገራትም ትልቅ ምሳሌ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የውሃን ሃብት በፍትሃዊና ምክንታዊ መርህ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው የብርሃን አማራጭ የሚሆን የጋራ ፕሮጀክት በመሆኑ ሁሉም ሊደግፈው ይገባል ብለዋል።