የዘንድሮው ምርጫ ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ነዉ – አቶ ርስቱ ይርዳው

አቶ ርስቱ ይርዳው

ሰኔ 15/2013 (ዋልታ) – የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የዘንድሮው ምርጫ ኢትዮጵያ ያሸነፈችበትና ለዴሞክራሲ መሰረት የተጣለበት በመሆኑ የእንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በመላው የክልሉ አካባቢዎች ምርጫው በሰላም መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የዘንድሮው ምርጫ ኢትዮጵያ ያሸነፈችበትና ለዴሞክራሲ መሰረት የሚጥል ምርጫ ማካሄድ መቻሉንም ነው የገለጹት።

ህዝቡም  ትናንትና ከለሊት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያ በመገኘት ድምፅ ለመስጠት ያደረገው ጥረት እጅግ የሚደነቅና ምስጋና የሚገባው ነው ብለዋል።

ሀገሪቱም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያካሄደችበት ምዕራፍ የታየበት ታሪካዊ ምርጫ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

በክልሉ ሲወዳደሩ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስታውቀዋል። ከምርጫው በኋላም በዚሁ መንገድ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።

በቀጣይም በሰላምና በልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መራጩን ህዝብ ጨምሮ የፀጥታ ኃይሉ፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ የምርጫ አስፈፃሚዎችና በምርጫው ሂደት ሚና የነበራቸው አካላት በሙሉ ምስጋና ይገባቸዋል ማለታቸውን ደሬቴድ ዘግቧል፡፡