የዘይት ፋብሪካው በግብዓት አቅርቦት ችግርና በመብራት መቆራረጥ የማምረት አቅሙ እየተስተጓጎለ ነው

መጋቢት 26/2014 (ዋልታ) ፊቤላ የዘይት ፋብሪካ በግብዓት አቅርቦት ችግርና በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ካለው የማምረት አቅም ከ40 በመቶ በታች እያመረተ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የዘይት አምራች ፋብሪካዎችን የመስክ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

በጉብኝቱ በቀን 1 ሚሊዮን 500 ሺሕ ሊትር ዘይት የማምረት አቅም ያለው ፊቤላ የዘይት ፋብሪካ በግብዓት አቅርቦት ችግርና በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ካለው የማምረት አቅም ከ40 በመቶ በታች እያመረተ መሆኑን የፋብሪካው ሥራ አስኪያጁ ሰለሞን ለገሰ ገልፀዋል፡፡

ፊቤላ ዘይት ፋብሪካ ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት ማስቆጠሩንና በዚህ ጊዜ ውስጥም ከ70 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት በማምረት ለኅብረተሰቡ እንዳሰራጨም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የደብሊው ኤ ዘይት ፋብሪካ በግብዓት አቅርቦትና በካፒታል እጥረት ምክንያት ካለው የማምረት አቅም እስከ 30 በመቶ ብቻ እያመረተ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ ሀሰን መሀመድ የመብራት እና የካፒታል እጥረት እንዲሁም የግብዓት አቅርቦት ችግሮች በአጭር ጊዜ ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ጥረት እንደሚደረግም አሰረድተዋል፡፡

አሁን እየተስተዋለ ያለውን የዘይት እጥረት ለመቅረፍ መንግሥት በልማት ድርጅቶች በቀጥታ ተገዝቶ እንዲቀርብ እያደረገ ነው ማለታቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 322 ባለሀብቶች በፍራንኮ ቫሉታ ያለቀለት የምግብ ዘይት እንዲያስገቡ እየተደረገ መሆኑንና ፍትሃዊ ስርጭት እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡