የደም ባንክ ኅብረተሰቡ ደም በመለገስ የሌሎችን ህይወት እንዲታደግ ጥሪ አቀረበ

ሀብታሙ ታዬ

ሚያዝያ 17/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ኅብረተሰቡ ደም በመለገስ የሌሎችን ህይወት እንዲታደግ ጥሪ አቀረበ፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ባለፉት ወራት በሁለቱ የእምነት ተከታዮች ዘንድ የነበረው የዐቢይ ፆም እና ረመዳን ወር ወቅቶች የደም ለጋሾችን ቁጥር መቀነሱን ገልጸዋል፡፡

ይህም በመላ ሀገሪቱ የደም እጥረት በከፍተኛ መጠን እንዲያጋጥም ማድረጉን አመልክተው ይሁን እንጂ ፆሞቹ ከተፈቱ በኋላ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም ግን በቂ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ መረጃ አገልግሎቱ እንደ ሀገር ባለፉት ዘጠኝ ወራት 343 ሺሕ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ 250 ሺሕ 235 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መቻሉን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም የአፈፃፀም ደረጃው 73 በመቶ መሆኑን አንስተው ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የደም ለጋሽ በጎ ፈቃደኞች በሚፈለገው ልክ አለመሳተፍ፣ አንዳንድ ደም ባንኮች በሙሉ አቅም ወደ ስራ አለመግባት፣ በበዓላት ወቅት ደም የመለገስ ሂደቱ አነስተኛ መሆንና መሰል ተግዳሮቶች እንዳጋጠመው ተናግረዋል፡፡

በአፈፃፀም ረገድ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሊያ ክልሎች የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገባቸውን ገልጸው ደቡብ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ እና ሌሎች ክልሎች ጉድለት እንደነበረባቸውም አመልክተዋል፡፡

በትግራይ ክልል የሚገኙ ሦስቱም የደም ባንኮች ስራ አቁመው እንደነበሩና አሁንም በሙሉ አቅም ወደ ስራ አለመግባታቸውን አንስተዋል፡፡

የነበሩ ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ ወራት የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝና ኅብረተሰቡም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አደባባዮች በሚገኙ ማዕከላት፣ በትምህርት ቤቶች፣ ቀይ መስቀል ግቢና በሁሉም የደም ባንክ መስሪያ ቤቶች ደም በበጎ ፈቃደኝነት መለገስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ህይወትን ማዳን ሰበብ የማይፈልግ በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ደም በመለገስ  የድርሻውን እንዲወጣም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው