የደቡብ ክልል ለመከላከያ ሰራዊት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ አደረገ

ታኅሣሥ 2/2014 (ዋልታ) የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የመከላከያ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት አስረክበዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በዚህ ወቅት ጥንት ኢትዮጵያዊያን አባቶች መስዋዕትነት በመክፈል ነጻነቷ የተጠበቀ አገር ማቆየታቸውን አስታውሰው የአሁኑ ትውልድም ለአገሩ ኅልውና አኩሪ ታሪክ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ለአገር ኅልውና እና ነጻነት ዘብ ለሆነው የመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ደጀንነት በተግባር እያሳዩ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ የማትንበረከክ እንዲሁም ነጻነቷን፣ ክብሯን እና ሉዓላዊነቷን አሳልፋ የማትስጥ አገር መሆኗን በተግባር ማረጋገጣቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ዛሬ ያደረገውን ድጋፍ ጨምሮ እስካሁን ባለው ሂደት ለሰራዊቱ ከ830 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉንም አመልክተዋል፡፡

የመከላከያ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል ተገኝ ለታ በበኩላቸው ኅብረተሰቡ እያከናወነ ያለው የደጀንነት ተግባር ሰራዊቱ ግዳጁን በድል እንዲወጣ የሞራል ስንቅ እንደሆነው ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ ለሰራዊቱ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።