የደቡብ ክልል ም/ቤት ከአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጋር የስልጣን ርክክብ አደረገ

ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) ነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ከአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጋር የስልጣን ርክክብ አደረገ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው የመጀመሪያ አስቸኳይ ጉባኤ በቅርቡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት 11ኛ ክልል ሆኖ ይፋዊ እውቅና ለተሰጠው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እውቅና በመስጠት ስልጣን አስረክቧል። ምክር ቤቱ ይህን የስልጣን ርክክብ ስርዓት የሚወስን የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

በዚህም የአምስቱ ዞኖችና የኮንታ ልዩ ወረዳ አፈ ጉባኤዎች ከደቡብ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ጋር የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።

አዲሱ ክልል የዳውሮ፣ ከፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ሸካ፣ ምዕራብ ኦሞ ዞኖችንና ኮንታ ልዩ ወረዳን በማቀፍ የተቋቋመ መሆኑ ይታወሳል።

የአዲሱ ክልል ተወካዮች የህዝቡ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ በማግኘቱ የተሰማቸውን ደስታ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

የአዲሱ ክልል ህዝቦች ሀገራችን የገጠማትን ፈታኝ ችግር ለማስወገድ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ይሆናሉ ሲሉም አረጋግጠዋል።

የአደረጃጀትና የመዋቅር ለውጥ እንጂ የህዝቦች በዘመናት የተገነባ የጋራ እሴቶችን በጋራ እናጎለብታለን ሲሉም ማናገራቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ምክር ቤቱ ከስልጣን ርክክቡ ቀደም ብሎ በሁለቱ ክልሎች መካከል ስለሚኖረው ቀጣይ ግንኙነትና የሀብትና ንብረት ክፍፍል በሚመለከት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ማጽደቁ ይታወቃል።