የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል

ነሐሴ 27/2013 (ዋልታ) የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በ200 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባውን ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል ለአገልግሎት ብቁ አደረገ።

በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ የተገነባው የመረጃ ማዕከልና ኔትዎርኪንግ ሲስተም ከዚህ በፊት በተማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረውን የትምህርት ክፍተት የሚያሻሽልና የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያሳድግ እንደሆነ ተገልጿል።

ከሁለት አመት በፊት የተጀመረው የዩኒቨርሲቲው የአይ ሲቲ ማዕከል በግቢው ውስጥ የነበረውን አነስተኛ የኢንተርኔትና ዲጂታል አገልግሎት ዘመናዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ከመጠናቀቁ በፊት የነበረው የአይሲቲና ኔትዎርክ አገልግሎት ለተማሪዎች አስቸጋሪና በመማር ማስተማሩም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደነበረው ተገልጿል፡፡

ከሁለተኛ ትውልድ ከፍተኛ ተቋማት መካከል የሚመደበው ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አሁን ላይ የዘረጋው የአይሲቲና ኢንተርኔት መሰረተ ልማት ዘመኑን የዋጀ ለመማር ማስተማር ሂደቱም ትልቅ ፋይዳ ያለው የሚባልለት ነው ተብሏል።

ማዕከሉ ከዚህ በፊት የነበረውን የአይሲቲ ውስንነት የሚቀርፍ ለሚቀጥሉት አስርት አመታት ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።

የመረጃ ማዕከልና ኔትዎርኪንግ ሲስተሙ 55 ዳታ ሴንተሮችና 50 የዋይርለስ ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ናቸው።

በተያያዘም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የአይሲቲ መሰረተ ልማት ፎረም አካሂዷል።

በፎረሙ ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው የአይሲቲ መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ለሌሎች ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰው፣ የፎረሙም አላማ እንዲህ አይነት ተሞክሮዎችን ለሌሎች ማካፋል መሆኑን ገልፀዋል።

ሀገሪቱ የዲጅታል ምጣኔ ሀበት ስትራቴጅ መንድፏን ተከትሎም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር፣ ምርምርና ጥናታቸውን በዲጂታል የታገዘ የማደረግ አሰራራቸውን እያጠናከሩ እንዲሄዱ ተገልጿል። ዘርፉን ለማሳደግም መንግስት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ እያፈሰሰ ይገኛል ነው የተባለው።

(በደምሰው በነበሩ)