የጀግንነት ቀን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ

ሹመቴ ይግዛው (ዶ/ር)

ጳጉሜ 4/2013 (ዋልታ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) የጀግንነት ቀንን አከበረ፡፡

የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ከ16 ሚሊየን ብር በላይ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለአገር መከላከያ ሰራዊት አበርክተዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ይግዛው (ዶ/ር) ጀግንነት በሁሉም መስክ በሁሉም ቦታ መሆን እንዳለበት ገልጸው፣ ፀኃይና ቁር ሳይበግረው የአገሩን ህልውና ለሚያስከብረው የአገር መከላከያ ሰራዊት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ጀግንነት የአንድ ወቅት ተግባር ባለመሆኑ የአባቶቻችንን ታሪክ በሁሉም መስክ በመጀገን ድህነትን ታሪክ ማድረግ አለብን ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ጀግንነት የኢትዮጵያውያን እሴት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢመደኤ ሰራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለአገር መከላከያ ሰራዊት ሲያበረክቱ ኩራት ይሰማቸዋልም ነው ያሉት፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በተቋሙ ሰራተኞች ስም ለአገር መከላከያ ሰራዊት የተደረገወን ድጋፍ ለመካላከያ ሚኒስትር ዴኤታዋ ማርታ ሉዊጂ አስረክበዋል፡፡

በሳሙኤል ሀጎስ