የጀግኖቻችን፣ የእሸቴዎችን አደራ በፍፁም አንረሳም – ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)  

ታኅሣሥ 1/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) “የጀግኖቻችን፣ የእሸቴዎችን አደራ በፍፁም አንረሳም” ሲሉ እሸቴ ሞገስ ከበኩር ልጁ ይታገስ እሸቴ ጋር ሆኖ ለሕዝቡና ለአገሩ የከፈለውን መስዋዕትነት የክልሉ መንግስት እንደማይረሳው ገልጸዋል።

የአሸባሪው ሕወሓት ኃይል የአማራ ክልልን ሲወር ክልላችን መቀበሪያው እንዲሆን ያደረጉት ጀግኖች እልፍ አእላፍ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በርካታ ጀግኖቻችን ከጠላት ጋር ተናንቀው ጀብዱ ሰርተዋል፤ ውድና ክብር መስዋዕትነት ከፍለዋል ብለዋል።

ከእነዚህም ለሕዝብና ለአገር ክብር ሲል ሞትን ንቆ ፊት ለፊት ገጥሞ ከእነ ልጁ በጀግንነት የክብር መስዋዕትነት የከፈለው የሸዋው እሸቴ ሞገስ አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።

እሸቴ ሞገስ ከበኩር ልጁ ይታገስ እሸቴ ጋር ሆኖ ለሕዝቡና ለአገሩ የከፈለው መስዋዕትነት፣ የሰራው ጀብዱ ብዙ ያስተምረናል፤ እሸቴ ሞገስ አልሸሽም ብሎ ከልጁ ጋር በርካታ ጠላትን ጥሎ በጀግንነት አልፏል ሲሉም አክለዋል።

እሸቴ ሞገስ በጀግንነት ሲዋጋ የወደቀው ልጁ አስከሬን ጥግ ሆኖ ሲዋጋ እሱም በክብር እንደሚሰዋ እርግጠኛ ሆኖ፣ እያለቀሰ ሳይሆን ለወገን የአርበኝነት ስንቅ በሚሆን አልበገር ባይነት ነው ብለዋል።

በርካቶች እንደ እሸቴ ሞገስ የክብር መስዋዕትነት ከፍለዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በየአካባቢው አስገራሚ አርበኝነት የፈፀሙ በርካታ እሸቴዎች እንዳሉን እሙን ነው፤ ወደፊትም ይኖራሉ ነው ያሉት።

እኛም የጀግኖቻችን፣ የእሸቴዎችን አደራ በፍፁም አንረሳም። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በዚህ የኅልውና ዘመቻ እንደ እሸቴ ሞገስ ለኅልውናቸው፣ ለሕዝብና ለአገራቸው ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን ቤተሰቦች በመንከባከብና በማገዝ አደራውን ይቀበላል ብለዋል።

ለጀግናው እሸቴ ሞገስ ቤተሰቦች ስለ መፅናናት አንነግራቸውም! ሌሎችም በክብር ሲወድቁ ስለመፅናናት አናነሳም ፤ እነ እሸቴ ሞገስ የልጅን ትኩስ አስከሬን ጥግ ሆኖ በሀዘን ሳይሆን በጀግንነት መፋለምን አስተምረውናል! ሲወርድ ሲዋረድ ስንዘክረው የኖርነውን የአባቶቻችን አርበኝነት በዘመናችን አሳይተውናል ሲሉም በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም ለሕዝባችንና ለአገራችን እስከመጨረሻው መስዋዕትነት እንድንፋለም የሰጡንን አደራ ተቀብለን ለኅልውናችን እስከመጨረሻው መስዋዕትነት እንታገላለን ብለዋል።