የጀግኖችን ቅርስ በማሠባሠብ ትውልድ እንዲማርበት ማድረግ ይገባል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

የካቲት 17/2015 (ዋልታ) ያለፉትንም ሆኑ አሁን ላይ ያሉ ጀግኖቻችንን የጀግንነት ማሳያ ቅርስ በመሠብሠብ ትውልዱ እንዲማርበት እና በቅብብሎሽ ለተተኪ እንዲተላለፉ የማድረግ ሥራ መሥራት ያሥፈልጋል ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህንን ያሉት ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የመከላከያ ወታደራዊ ቅርስ ጥበቃ እና ሙዚየም ዳይሬክቶሬትን በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡

የዘንድሮውን 127ኛ የአድዋ ድል በዓል በመሪነት የሚያከብረውና ኃላፊነቱን ወስዶ እየተንቀሳቀሰ ያለው መከላከያ በመሆኑ የመከላከያ ወታደራዊ ቅርስ ጥበቃ እና ሙዚየም ዳይሬክቶሬት ትኩረት ሠጥቶ በባለቤትነት ሥሜት መንቀሳቀስ እንዳለበትም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

የመከላከያ ወታደራዊ ቅርስ ጥበቃ እና ሙዚየም ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዱልቃድር ደባሹ በበኩላቸው ወታደራዊ ቅርሶች ተለይተው እና ለምተው ጥናት ተደርጎባቸው ዘመናዊ ሠራዊት መገንባት በሚቻሉበት አግባብ ለተቋሙና ለሀገር በሚጠቅሙበት ሁኔታ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ከ500 በላይ ወታደራዊ ቅርሶች ማህተሞች እና ቲተሮችን እንዲሁም ሌሎች ቅርሶችን የማሠባሠብ ሥራ መሠራቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ ቅርሶችን ቀጣይ በሚገነባው ሙዚየም ለማካተት በጥረት እየተሠራ ነው ማለታቸውን ከሰራዊቱ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡