የገቢዎች ቢሮ የግብር ከፋዮችን የቤት ለቤት ጉብኝት ፕሮግራም ይፋ አደረገ

የግብር ከፋዮችን የቤት ለቤት ጉብኝት

ኅዳር 30/2014 (ዋልታ) በግብር ሰብሳቢውና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል እያደገ ያለውን በጎ ግንኙነት ይበልጥ ለማሻሻል ያለመ የግብር ከፋዮች የቤት ለቤት ጉብኝት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ይፋ ሆነ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ባለፉት አራት ወራት 25 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ የዕቅዱን 118 በመቶ ማሳካቱ ተጠቁሟል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ሙሉጌታ ተፈራ በግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤትና በግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ዘንድ ቀደም ሲል የነበረው ግንኙነት ባለመተማመን ላይ የተመሰረተ እንደነበር አስታውሰው ይህም የአንድ አካል አጥፊ አተያይ መሆኑን በቅጡ በመረዳት የነበረውን እሳቤ የመቀየር ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

ቢሮው የግብር ከፋዮች የቤት ለቤት ጉብኝት ፕሮግራም ባስጀመረበት ወቅት በተመረጡ የደረጃ ‹‹ሀ፣ ለ እና ሐ›› ግብር ከፋዮች ዘንድ የቤት ለቤት የሥራ ቦታ ጉብኝት ተደርጓል።

ጉብኝት የተደረገባቸው ግብር ከፋዮች ግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ግብር ከፋዩን ማኅበረሰብ በጥርጣሬ ከማየት አልፎ በዚህ ደረጃ መቀራረብ መፈጠሩ የሚበረታታ ነው ማለታቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።