የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከሳውዲ ባለሥልጣናት ጋር ተወያዩ

ጥር 20/2014 (ዋልታ) በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራው የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን ከሳውዲ አረቢያ የንጉስ ሰልማን የሰብኣዊ እርዳታ ማእከል የበላይ ኃላፊ አብዱላህ አልራቢሀ (ዶ/ር) ጋር በሁለቱ አገራት የጋራ ሰብኣዊና የእርዳታ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በተመሳሳይ ሚኒስትሩ ከሳውዲ ልማት ፈንድ ሥራ አስኪያጅ ሱልጣን አልማርሻድ ጋርም ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን በሳውዲ ልማት ፈንድ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ የሚያካሂዱትን የልማት ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ያሉበትን ሁኔታ በጋራ ገምግመዋል፡፡
በሳውዲ ልማት ፈንድ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች በመሰረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት በአገሪቱ ማኅበራዊ አገልግሎትና በኢኮኖሚ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጾኦ እንዳላቸው አመልከተዋል፡፡
ሳውዲ አረቢያ በሰብኣዊ እርዳታና በኢኮኖሚ ልማት ለምታደርገው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን መግለፃቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡