የጠ/ሚ/ሩ የደኅንነት አማካሪ የወርቅ እና ውሃ ፈላጊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጥምረት እንደማይሳካ ገለፁ

ኅዳር 22/2014 (ዋልታ) የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው የወርቅ እና ውሃ ፈላጊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጥምረት እንደማይሳካ ገለፁ፡፡
ከሰሞኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠረፍ አካባቢ ቅኝት ያደረጉትና በስፍራዎቹ ከሚገኘው በርታ ማኅበረሰብ አባላት ጋር የነበራቸውን ውይይት ተከትሎ ነው ይህን ያሉት፡፡
አማካሪው በኅልውና ዘመቻ ታላቁን የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ ለማስተጓጎል ከሱዳን በኩል የሚገቡ ሰርጎገቦች ከሚመነጥረው የመከላከያ ሰራዊትና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታ ኃይል ጋር በተንቀሳቀሱበት ወቅት ከበርታ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ሕዝቡ የወርቅ እና ውሃ ፈላጊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጥምረት በቤኒሻንጉል በኩል ኢትዮጵያን ለማወክ የሚያደርጉት ጥረት እንደማይሳካና አሁን በወርቁም በውሃውም እኛው መጠቀም ጀምረናል ማለታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከእኛው ጋር በውሃውም በወርቁ ለመጠቀም የሚፈልግ ካለ መጀመሪያ ኢትዮጵያን ያክብር፤ ከዚያ ውጭ ፈፅሞ አይሳካም ብለዋል፡፡
የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶች ሊያውቁት የሚገባው ጉዳይ ቢኖር አገራችን ታፍራና ተከብራ በነፃነት ፀንታ የኖረችው በሚጠሏት ኃይሎች በጎ ፈቃደኝነት ሳይሆን በውድ ልጆቿ ክቡር መስዋዕትነት መሆኑን ያነሱት የአካባቢው ነዋሪዎች ሞተን ካላለቅን በርታን ተራምዶ ኢትዮጵያን መጉዳት አይታሰብም ማለታቸውንም አክለዋል፡፡
በተግባርም የቅጥረኝነት ተልዕኮ ይዞ የመጣን ኃይል መንጥረው እንደሚሆን አድርገውታል ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪው ከአሁን በኋላ ከሱዳን እየተነሱ ኢትዮጵያን መውጋት ይበቃል ሲሉም አመልክተዋል፡፡