የጣይቱ የባህል እና የትምህርት ማዕከል በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው

የካቲት 18፣ 2013 (ዋልታ) –  ህዳር 3 ቀን 2011ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠውን የቀድሞ ሃ/ ጊዮርጊስ ወ/ሚካኤል መኖሪያ ቤት በመረከብ የባህል እና ትምህርት ማዕከልነት ለመመስረት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል።
117 አመት እድሜ ባለፀጋ የሆነውን ይህንን ታሪካዊ ቤት ቅርስነቱን እንደጠበቀ አስጠግኖ ለአገልግሎት ለማብቃት የጥናት እና የዲዛይን ስራው መጠናቀቁ ነው የተነገረው።
ማዕከሉ ለአገልግሎት ሲበቃ የኪነ ጥበብ ባለሙያዋች ምርምር የሚያደርጉበት፣ ለስነ ጥበብ ፍላጎት ያላቸው ሁሉ የሚሰለጥኑበት፣ የኢትዮጵያውያን ባህል እና ቋንቋ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገርበት በይበልጥም በበርካታ ቱሪስቶች የሚጎበኝ ይሆናል ተብሏል።
ላለፉት 20 አመታት በሰሜን አሜሪካ ተመስርቶ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ባህል ላይ በስፋት ሲሰራ የነበረው የጣይቱ የባህል እና ትምህርት ማዕከል ከዚህ ቀደም 110 የሚደርሱ ወጣቶችን በአሜሪካ ለማሰልጠን ችሏል ያለችው የማዕከሉ መስራች አርቲስት አለምፀሀይ ወዳጆ፣ ተቋሙ በሰራው ስራ ከ56 የሚበልጡ ሽልማቶችን ማግኘት ችሏል ብላለች።
መጋቢት 4 ቀን 2013 በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ ለታሪክ የሚቆረቆሩ ሁሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተጠይቋል።
(በቁምነገር አህመድ)