የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለሀገር አንድነት ጠንቅ መሆናቸው ተገለፀ

ሰኔ 22/2014 (ዋልታ) የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት በሕዝቦች ዘንድ ያሉ መልካም እሴቶችን በመሸርሸር ለሀገር አንድነት ጠንቅ መሆናቸው ተገለፀ።
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አዘጋጅነት “የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃን እየታገልን ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ የዲሞክራሲያ ልምምድ ላይ ትገኛለች ያሉ ሲሆን በሀገሪቱ የዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማጎልበት እንዲህ ያሉ የውይይት መድረኮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ለፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ለአገራዊ አንድነትና ለሰብዓዊ ክብር ጠንቅ በመሆኑ ኃላፊነት የጎደላቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ስርዓት ለማስያዝ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ቁጥጥር በእጅጉ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሰዎች ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብአዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደኅንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ማስቻል እንደሚገባም ገልፀዋል።
ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት አደጋ የሆኑ የጥላቻ አመለካከትና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት መስፋፋትንና ተያያዥ ወንጀሎችን መከላከልና መቀነስ የሁሉም አካላት ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ያለበት ደረጃ፣ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ያለበት ደረጃ እና የሙያ ማኅበራት ሚና፣ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ያሉ የሕግ ማዕቀፎች ሁኔታ የሚሉ ጉዳዮች በመድረኩ ውይይት እየተካሄደባቸው ነው።
በደረሰ አማረ