የጥቅምት 24 ሰማዕታት ቀን በደቡብ ሱዳን ታስቦ ዋለ

ጥቅምት 25/2014 (ዋልታ) ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአሸባሪው ሕወሐት ለተሰው የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት አባላት የሰማዕታት ቀን  በደቡብ ሱዳን ጁባ  በኢትዮጵያ ኤምባሲ ታስቦ ዋለ፡፡

ዝክረ ሰማዕታቱ የታሰበው “ክብር ኢትዮጵያን ሲሉ ለተሰዉ ጀግኖቻችን” በሚል መሪ ሀሳብ መሆኑ ተመላክቷል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት አምባሳደር ነቢል ማህዲ  ከ20 ዓመታት በላይ ከቤቱና ከቤተሰቡ ተነጥሎ ጠላት ሲመጣ የሚመክት፣ አዝመራ ሲደርስ የሚያጭድ፣ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋማትን በራሱ ገቢ ይገነባ የነበረን ሠራዊት ሰዋዊ ባልሆነ መልኩ በአሸባሪው ሕወሓት የተሰጠው  ምላሽ በታሪክ የማይዘነጋ መሆኑን ገልጸዋል።   የተከፈለው መስዋዕትነት  ዋና ዓላማም የኢትዮጵያን  ሉአላዊነት ለማስከበር ነው ብለዋል።

ጁንታው በተላላኪነት የወሰደው ሀገር የማፍረስ አጀንዳን ለመቀልበስ በዚህ ወሳኝ ወቅት አንድነታችንን በመጠበቅ፣ የገባነውን ቃል በማደስ፣ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይገባናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ የኤምባሲው ሠራተኞች፣ የሚሊቴሪ አታሼና ተጋባዥ እንግዶች መገኘታቸውን ጁባ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።