የጦር ኃይላችንን ለጦርነት የምናዘጋጀው ሰላምን በመጥላት ሳይሆን ሰላምን ለማረጋገጥ ነው – ሌ/ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ

ሰኔ 18/2014 (ዋልታ) “ሁላችንም ጦር ኃይላችንን ለጦርነት የምናዘጋጀው ሰላምን በመጥላት ሳይሆን ሰላምን ለማረጋገጥ ነው” ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ተወካይ እና የመከላከያ የሜካናይዝድ ማስተባበሪያ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ተናገሩ፡፡
ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ይህንን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የመከላከያ ሚኒስቴር ተቀማጭነታቸውን አዲስ አባባ ላደረጉ ወታደራዊ አታሼዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ ነው፡፡
ሌተናል ጄኔራሉ ሉላዊነት ባስተሳሰረው ዓለም ውስጥ መደጋገፍና አብሮነት ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
“ሁላችንም ጦር ኃይላችንን ለጦርነት የምናዘጋጀው ሰላምን በመጥላት ሳይሆን ሰላምን ለማረጋገጥ ነው” በማለት ገልጸው፤ ይህም የአገርን ሉዓለዊነት እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር እንደሆነ አንስተዋል።
ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ ችግር ቢገጥማቸው እንኳን በታሪካቸው የውጭ ወራሪዎች ሲነሱ በጋራ ተነስተው ለአገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት እንደሚቆሙ በተደጋጋሚ እንዳሳዩ አስታውሰዋል።
በዓለም ላይ ጦርነት መነሻው ቀላል ቢሆንም ማብቂያውን ግን አዳጋች ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ ለሰላም፣ ለልማትና ትብብር ቀዳሚ ጉዳይ አድርገን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
የዓለም ሕዝብ ለሰላም፣ ለልማት እና ለፀረ-ድህነት ትግል ድምፁን ከፍ አድርጎ እያሰማ እንደሆነ ገልጸው ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ሰላም ካልተረጋገጠ ልማት ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ መረዳት አለበት ነው ያሉት።
በመሆኑም በሁሉም የዓለም ክፍል ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን ሁላችንም በትብብር መስራት አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በመተማመን ላይ በመመስረት ከዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰቡ ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ብዛት ያላቸው ሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በየሳምንቱ ርዳታ እያጓጓዙ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
የተወሰኑ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የተዛባ መረጃ በማሰራጨት የመንግሥትን መልካም ተግባር ጥላሸት መቀባታቸው ትክክል አለመሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመሆኑም ዓለም ዐቀፉ ማኅብረሰብ ከትግራይ በተጨማሪ በአማራና አፋር ክልሎች ያሉ ወገኖች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መረዳት እንዳለበት ጠቅሰው ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችም የኢትዮጵያን ህግ መሰረት ባደረገ አግባብ እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል።
መንግሥት ለሰላማዊ አማራጮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ የተናገሩት አምባሳደር ዲና በጦርነቱ የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ካሉ የሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።