መስከረም 21/2017 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የፀጥታና ደህንነት አካላት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን ገለጸ፡፡
የፀጥታና ደህንነት አካላት የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም መጠናቀቁን አስመልክተው በዛሬው ዕለት ባደረጉት ግምገማ ላይ የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
መስከረም 25 እና 26 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ የሚከበሩት የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓላት ባህላዊ ስርዓታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ኃይል ተሰማርቶ ወደ ስራ መገባቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢሬቻ በዓል ከሚፈቅደው ባህላዊ ስርዓት ተቃራኒ የሆኑ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችና መልዕክቶችን ይዞ መገኘት ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑን ያሳሰቡት የፀጥታና ደህንነት አካላት በዓሉን ለእኩይ ዓላማ ለመጠቀም የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ተግባራት በፍፁም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህንን በመተላለፍ በዓሉን ለማወክ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም ግለሰብና ቡድን ላይ ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲመለከት የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (EFPApp) ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመጠቀም ጥቆማዎችን እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡