የፊንጫ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 740 ጊጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት አቅዷል

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) የፊንጫ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ2015 በጀት ዓመት 740 ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ማቀዱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት አስታወቀ።

በጽ/ቤቱ የፕላኒንግ ሥራ አስኪያጅ ጥሩወርቅ ሽፈራው እንደገለፁት የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ግድብ ኃይል ለማመንጨት የሚያስፈልገውን ውሃ በመገባደድ ላይ ባለው የክረምት ወራት ሙሉ ለሙሉ የያዘ ሲሆን ይህም ዕቅዱን ለማሳካት ያስችለዋል ነው ያሉት፡፡

የኃይል ማመንጫው እያንዳንዳቸው 33 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው አራት ተርባይኖች ሲኖሩት በሶስቱ ተርባይኖች 100 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ላይ ይገኛል፡፡

አንደኛው ተርባይን ለጊዜው በጥገና ሥራ ምክንያት የቆመ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት የጥገና ሥራውን የሚጀመር እንደሚሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል መረጃ ያመለክታል።

የፊንጫ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአሮሚያ ብሔራዊ ከልላዊ መንግስት ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ይገኛል፡፡