የፋይናንስ አቅርቦትና አስተዳደር ችግር ለግብርና ዕድገት ማነቆ መሆኑ ተገለጸ

የፋይናንስ አቅርቦትና አስተዳደር ችግር ለግብርና ዘርፍ ዕድገት ማነቆ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ “የገጠር የፋይናንስ አቅርቦት ለግብርናው ዕድገት” በሚል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን ከግብርናው ዕድገት መሰናክሎች የፋይናንስ ተቋማት የብድር አቅርቦትና ከመንግስት የሚመደበው በጀት ማነስ ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ባንኮች ለማበደር ያስቀመጧቸው የመሬት ደረጃዎች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ በመሆናቸው በዘርፉ ለተሰማሩና መሰማራት ለሚፈልጉ ብድር ለማግኘት ማነቆ ሆኗል ብለዋል።

የወጡ ፖሊሲዎች በአግባቡ እንደማይተገበሩና ባንኮችም ለዘርፉ በበቂ ሁኔታ ብድር የማመቻቸት ችግሮች እንዳሉባቸው ሚኒስትሩ መጠቆማቸውን ከኢዜአ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።

ሚኒስትሩ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እያደገ የመጣውን የአገሪቷን የምርት ፍላጎት ለማሟላትና የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት አማራጭ የፋይናንስ ተቋማትና የተሻለ አስተዳደር ይፈልጋል ብለዋል፡፡