የፌደራል መንግሥት መግለጫና ጥሪ

ጥቅምት 12/2014 (ዋልታ) ሕብረተሰቡ የሕወሓትን የሽብር ቡድን እኩይ ዓላማና እቅድ በመረዳት አገርን ለመበታተን የተነሳውን የጥፋት ኃይል ሴራ እንዲያከሽፍ መንግሥት ጥሪ አቀረበ፡፡
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥቷል።
ሙሉ መግለጫው ቀጥሎ ቀርቧል:-
አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ደሴ ከተማን ዒላማው አድርጎ የሚያቅዳቸው በርካታ የጥፋት ሥራዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው።
በሁሉም ግንባሮች በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ለህልውናቸው በተሰለፉት የክልሉ ወጣቶች የሚደርስበት ከባድ ኪሳራ ሩቅ እንደማያስኬደው ግልጽ ሆኗል።
የደሴ ከተማ ላይ ያቀደው ጥፋትም ይህንኑ ሽንፈቱን በጥፋት ሥራ ለመሸፈን ማቀዱን ያሳያል። ኅብረተሰቡም የዚህን ሽብር ቡድን እኩይ ዓላማና እቅድ በመረዳት ሀገርን ለመበታተን አቅዶ የተነሳውን የጥፋት ኃይል ሴራ ማክሸፍ ይገባዋል።
የሽንፈት ገፈትን እየቀመሰ የሚገኘው የሽብርተኛው ቡድን በደሴ ብዙ ሠራዊት ሊኖር ይችላል በሚል በተጨማሪም ፋኖ የከተማ የውጊያ ስልትን ለማካሄድ ሊዘጋጅ ይችላል የሚል ግምትን በማሳደር ሰርጎ ገቦችን በመጠቀም በከተማዋ የመብራት መስመሮችን ለማቋረጥ እና በደሴ የሚገኘው የፀጥታ ኃይል ላይ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለማሳደር ማቀዱን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።
በከተማዋ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊትም ኾነ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከመረጃ እንዲርቅ ማድረግንም በእቅዱ ይዟል። ሐሰተኛ መረጃዎችንና ምስሎችን በስፋት በማሰራጨትም የሠራዊቱንና አጠቃላይ የፀጥታ ኃይሉን ሞራል ለማዳከም ያስችሉኛል በሚል የያዛቸው እቅዶች መኖራቸው ተደርሶበታል።
ይህ የጥፋት ቡድን ሀገርን ማሸበር ዋና ዓላማው መሆኑን የሚያሳይ ነው። የአማራ ክልል ሕዝብና መላው ኢትዮጵያውያን የሽብር ቡድኑ ትህነግ ያቀዳቸውን የማወናበጃና የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተግባራት የማወክ እንቅስቃሴን ቀድሞ በመረዳት ሰርጎ ገቦችን በማጋለጥና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ እንደስካሁኑ ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት መልእክት ያስተላልፋል።
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት፦
የአማርኛ ፌስቡክ ገፃችንን ይወዳጁ ይከተሉ
ከአረብኛ ፌስቡክ ገፃችን ጋርም ይጓዙ
የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
የትዊተር ገፃችንን ይከተሉ
አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!