የፌዴሬሽን ም/ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው

ጥቅምት 1/2015 (ዋልታ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን 2ኛ የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።

የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የ2015 እቅድ አቅርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

በ2015 ዓ.ም ነፃ ተቋም መመስረትና ማደራጀት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ነው ቋሚ ኮሚቴው ያስታወቀው።

በተጨማሪ የምክር ቤቱን አቅም ማጠናከር ላይ በትኩረት ይሰራል ተብሏል።

የድጎማ በጀት ቀመር ለመስራት የህዝብና ቤት ቆጠራ መስራት አስፈላጊ እንደሆነም ነው በውይይቱ ወቅት የተገለፀው።

በተጨማሪም የመሰረተ ልማት በጀት ክትትል ላይም በትኩረት ይሰራል ተብሏል።

የበጀት ቀመሩን ለማዘጋጀት ከክልልና ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እንደሚሰራም ተገልጿል።

ምክር ቤቱ የድጎማና በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የ2015 እቅድ በ112 ድምፅ አፀድቋል።

ቋሚ ኮሚቴው በፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት በትኩረት እንደሚሰራና የክልሎች ገቢ ማጠናከር ላይ እንደሚሰራ ተመላክቷል።

የማንነት ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ የ2015 ዓ.ም እቅድ እያቀረበ ሲሆን ህብረ ብሄራዊ አገራዊ አንድነት ግንባታን በማጎልበት የአስተዳደርና ወሰን ጥያቄዎች እንዲፈቱ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል።

የማንነት ጥያቄዎችን በጥናትና አሳታፊ በሆነ ውይይት ለመፍታት እንደሚሰራም ነው የገለፀው።

በቀረበው እቅድ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ውይይት እያደረጉ ሲሆን የሰላም ግንባታ የማንነት አስተዳደር ወሰን ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባም ነው የገለፁት።

ጥያቄዎቹ በጥናት ላይ ሊመሰረቱ እንደሚገባም ነው የምክር ቤቱ አባላት የተናገሩት።

በሱራፌል መንግስቴ