የፑሽኪን አደባባይ – ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ግንባታን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታወቀ

 

 

ከአሌክሳንደር ፑሽኪን አደባባይ በጎፋ ማዞሪያ ጎተራ ማሳለጫ ድረስ እየተሰራ የሚገኘው የመንገድ ፕሮጀክት የግንባታ ስራውን በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቅ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ የመንገድ ፕሮጀክቱን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ከአቶ ዣንጥራር አባይ እና ከሌሎች የስራ ሀላፊዎች ጋር ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እንደገለፁት አሁን ላይ የዋሻ ቁፋሮ ስራን ጨምሮ ግንባታው በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከፑሽኪን እስከ ጎተራ ድረስ ያለው ዋና መንገድ በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ኢንጂነር ሞገስ በመጪው ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ ደግሞ ከቄራ ወደ ጎፋ ማዞሪያ የሚወስደውን የማሳለጫ ድልድይ ለማጠናቀቅ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 3.8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ30 እስከ 45 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ያለው ሲሆን የግንባታ ስራውን ቻይና ፈርስት ሀይ ዌይ ኢንጂነሪንግ የተባለ የስራ ተቋራጭ እያከናወነው ይገኛል፡፡

ቤስት አማካሪ ድርጅት ደግሞ የግንባታ ቁጥጥሩንና የማማከር ስራውን እያከናወነው የሚገኝ ሲሆን ለግንባታ ወጪውም ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦለታል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ በሁለት በኩል 320 ሜትር ርዝመት ያለው ዋሻ፣ የፈጣን አውቶብስ መተላላፊያ መስመርን ጨምሮ ከስርና ከላይ 100 ሜትር ርዝመት ያለው ማሳለጫ እንዲሁም ስድስት ሜትር የሚረዝም የእግረኛ መንገድን አካቶ እየተገነባ ሲሆን አሁን ላይም 50 ከመቶ በላይ የግንባታ ስራው ተጠናቋል፡፡

(ምንጭ፡- አዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን )