የፖለቲካ ፓርቲዎች በማኒፌስቷቸው ለኢትዮጵያ ሰራተኞች የሰጡት ትኩረት አናሳ ነው ተባለ

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – የፖለቲካ ፓርቲዎች በማኒፌስቷቸው ለኢትዮጵያ ሰራተኞች የሰጡት ትኩረት አናሳ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰራተኞች መብቶች ተሟጋች ድርጅት አስታወቀ።

የሰራተኛው መብት በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ላይ የተሰጠውን ትኩረት የተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ ለኢትዮጵያ ሰራተኞች መብቶች ተገቢውን ትኩረት አልሰጡም ተብሏል።

ምክክሩ የተዘጋጀው በሁለት ጥናታዊ ፅሁፍ ውጤቶች ላይ በመመርኮዝ እንደሆነ የተናገሩት የኢትዮጵያ ሰራተኞች መብቶች ተሟጋች ድርጅት ዳይሬክተር አሸናፊ ግዛው፣ ጥናቶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰራተኞች ተገቢውን ትኩረት እንዳልሰጡ ያመላክታሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን ምክትል ዳይሬክተር አያሌው አህመድ በበኩላቸው፣ በጥናቱ እንደተመላከተው በፓርቲዎች ማኒፌስቶ የሰራተኛው መብት 80 በመቶ ያህል ትኩረት እንዳልተሰጠው ጠቁመዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ሰራተኞች መብትና ጥቅም ከማስከበር አኳያ የተሻለ ሀሳብ ይዘው እየቀረቡ ላለመሆኑ አመላካች እንደሆነና የሰራተኛውን ህይወት የሚቀይር ግልፅ አቋሞቻቸውን ቢያቀርቡ የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል።

በጥናቱ የተካተቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ውይይቱ ማኒፌስቷቸውን ከሰራተኛው አንፃር እንዲመለከቱ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በማኒፌስቷቸው፣ በፖሊሲዎቻቸውና ፕሮግራሞቻቸው ለኢትዮጵያ ሰራተኞች ዝቅተኛ ክፍያ ወለል ማበጀት፣ የስራ አጥነት ቁጥር ቅነሳና ሌሎች የሰራተኛው መብቶች ላይ ያላቸውን አቋሞች ሊያሳውቁ እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡

(በደረሰ አማረ)