የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክት የመምረጥ ተግባር ተጀመረ

ከጥር 13 እስከ 24 ድረስ የሚካሔደው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክት የመምረጥ ተግባር መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ቦርዱ ለፓርቲዎቹ ካዘጋጃቸው የምልክት አልበሞች ውስጥ ፖርቲዎቹ የፈለጉትን መምረጥ የሚችሉ ሲሆን፣ ከተዘጋጁት ውጪ ምርጫ ቦርድ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች የሚያሟላ የራሳቸውንም ምልክት በማምጣት መመዝገብ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

የቦርድ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶሊያና ሽመልስ ህጋዊ ሠውነት ካገኙ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች 25ቱ ይሆነናል ያሉትን ምልክቶች በአንድ ቀን ብቻ መምረጣቸውን ገልፀዋል።

አንዱ የመረጠውን ሌላው መምረጥ እንደማይችልም የጠቆሙት ወ/ሪት ሶልያና፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች የሚመርጡት ምልክት ለምርጫው ጊዜ ብቻ የሚያገለግል መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከጥር 13 እስከ 18 ምልክቶቹን የመምረጥ ስራ ተጠናቆ ከጥር 18 እስከ 24 ድረስ ባለው ጊዜ ምርጫ ቦርድ የተመረጡትን ምልክቶች አጣርቶ ይፋ እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡

(በድልአብ ለማ)