የ2016 በጀት ዓመት 801.65 ቢሊየን ብር ሆኖ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀረበ

ሰኔ 1/2015 (ዋልታ) የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት አጠቃላይ በጀት 801.65 ሆኖ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ 24ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን በ2016 ዓ.ም በጀት ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም አጠቃላይ የ2016 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት በጀት 801.65 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 370.14 ቢሊየን ለመደበኛ፣ 203.44 ቢሊየን ለካፒታል፣ 214.07 ቢሊየን ለክልሎች ድጋፍና 14 ቢሊየን ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ሆኖ መያዙ ተጠቁሟል፡፡

ባለፉት ጊዜያት በሀገሪቱ ለደረሱ ተቋማትና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች 20 ቢሊየን ብር በጀት መያዙም ተገልጿል።

የ2016 በጀት ዓመት ለፌደራል መንግሰት በጀት የቀረበው 801.65 ቢሊየን ብር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ1.9 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተመላክቷል፡፡

ለ2016 በጀት ዓመት ጠቅላላ ገቢ የውጭ እርዳታን ጨምሮ 520.6 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ቢሆንም የ281.05 ቢሊየን ብር የበጀት ጉድለት እንዳጋጠመው ተገልጿል፡፡ ይህንን ጉድለትም በብድር ለመሸፈን ታቅዷል ነው የተባለው፡፡

ባለፉት ዓመታት እንደሀገር ያጋጠመ የውስጥ ግጭትና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ኢኮኖሚው የሚጠበቅበትን እንዳያመነጭ አድርጓል የተባለ ሲሆን የሰሜኑ ጦርነት ከልማት አጋሮች ጋር ይሰራ ለነበረው ስራ እክል ፈጥሮ እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በጀትን በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል የተለያዩ የፋይናስ መቆጣጠርያ መንገዶች መዘርጋቱ ተገልፆ ተቋማት የሚደርሳቸውን በጀት ቆጥበው ሊጠቀሙ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

ለመደበኛ ከተያዘው በጀት ላይ 81.8 በመቶ የሚሆነው ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ይሆናል የተባለ ሲሆን በበጀት ዓመቱ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ ላይ ብቻ ትኩረት እንደሚደረግና አዲስ የሚጀመር ፕሮጀክት እንደሌለ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ሀገሪቱ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ አንጻር በ2016 በጀት ዓመት የመንግስት መስሪያ ቤቶች አዲስ ሰራተኛ እንደማይቀጥሩ ተገልጿል፡፡ ሆኖም ግን የግሉ ዘርፍ የስራ እድል መፍጠር እንዲችል ድጋፍ ይደረጋል ተብሏል።

የቀረበው ረቂቅ በጀት ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመራቱም ተገልጿል፡፡

በመስከረም ቸርነት