ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራ ነው

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ እስቴት ዩኒቨርሲቲ በ2020 ዓ.ም የስልጠና፣ ትምህርትና አማካሪነት ባለሙያ ማዕከል እንዲሁም በጥናትና ምርምር አፍሪካ ውስጥ ተወዳዳሪና ተመራጭ ለመሆን ተልዕኮ አንግቦ እየሰራ መሆኑ ተገለጸ።

ለኦሮሚያ ሕዝብ ጥቅም ታስቦ በክልሉ መንግሥት የተመሰረተው ዩኒቨርሲቲው በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ገረሞ ሁሉቃ (ዶ/ር) የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የራሱን ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የወሰነው ውሳኔ ጠንካራና አስፈላጊ ውሳኔ ነበር ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ዋና ጊቢ በባቱ ከተማ እንደሚገኝ ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲውን ለማስፋፋት ሁለት ቅርንጫፎች በአዲስ አበባና በአዳማ ከተማ መኖራቸውን አስታውቀዋል።

በ2009 ዓ.ም የተመሰረተው የኦሮሚያ እስቴት ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን ከመከወን ባለፈ የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠትና የሕዝብን ጥቅም መሰረት ያደረጉ አገልግሎቶች ላይ በማተኮር እየሰራ ይገኛል ተብሏል።

ዩኒቨርሲቲው በመጪዎቹ አስርት ዓመታት ለክልሉ ማኅበረሰብ በይበልጥ በመቅረብ እንደሚሰራ ተመላክቷል።