ዩኒቨርሲቲዎች ለሕልውና ዘመቻው 8 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረ

ነሀሴ 07/2013 (ዋልታ) – በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ለሕልውና ዘመቻው 8 ሚሊየን ብር የሚገመት ልዩ ልዩ ድጋፍም አድርገዋል፡፡

ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ፣ ቦንጋ፣ ጅማ፣ ወልቂጤ፣ መቱ፣ ዋቻሞ፣ ወለጋ እና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው ድጋፉን ያደረጉት፡፡

ተቋማቱ በህልውና ዘመቻው ከፍተኛ ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኘውን ደባርቅ ሆስፒታልን ለማጠናከር የሕክምና ቁሳቁስ፣ ልዩ ልዩ መድኃኒቶች እና የምግብ እህል ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ድጋፉን ለማስረከብ የቦንጋ የወልቂጤና የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮችም ተገኝተዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር  ጀማል አባፊጣ፣ ኢትዮጵያውያን ተገድደን በገባንበት የሕልውና ጦርነት ፊት ለፊት ተጋፍጦ በጀግንነት እየተፋለመ ለሚገኘው ሕዝባችን አጋርነት ለማሳየት ተገኝተናል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ለሕልውና ዘመቻው የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

የህልውና ትግሉ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ጦርነቱ የሚያስከትለውን ጉዳት በመታደግና በሙያ የመደገፍ ድርብ ኀላፊነት አለባቸው ያሉት ዶክተር ጀማል፥ በአካባቢው ተቋማቱ ይህንን ሲያከናወኑ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩ በአካባቢው ላሉ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ የሚተው ባለመኾኑ ተቋማቱ አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችና ሆስፒታሎች ለሕልውና ዘመቻው በሙሉ አቅማቸው እንዲሠሩ ድጋፉ በመጠኑም ቢኾን እንደሚያግዝ ነው ዶክተር ጀማል የተናገሩት፡፡

የዩኒቨርሲቲዎቹ የአጋርነት ድጋፍ ከክልላዊ የዩኒቨርሲቲ አደረጃጀት የተሻገረ የአጋርነት ትስስር መስርቷል፥ ይህም ርቀት ሳይገድባቸው ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ለሀገራዊ ዓላማ የተሰባሰቡ መኾኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ድጋፉ ከተቋማዊ አጋርነት ባለፈ የሕዝብ ለሕዝብ አንድነትን ያጠናክራል ያሉት ዶክተር ጀማል፥ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት የድጋፍና የአብሮነት ተግባር እንዲፈጽሙ የሚያነሳሳ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት መልዕክት በሁሉም ቦታ የሁላችንም ደኅንነት እስካልተረጋገጠ ድረስ የእያንዳንዳችን ደኅንነት ሊረጋገጥ አይችልምና የተጋረጠብንን ሀገራዊ የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ በጋራ እንሥራ ብለዋል፡፡

የደባርቅ፣ የጎንደርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ላደረገላቸው አቀባበል፣ ላሳያቸው ፍቅር እና እንክብካቤ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶችና ተወካዮችም የውጪ ጠላትና የውስጥ ባንዳዎች በተቀናጀና በተናበበ መልኩ የሀገር ሉዓላዊነትን እየተፈታተኑ መኾኑን አንስተዋል፡፡

ተከብሮ የኖረው የሀገር ሉዓላዊነት እና ክብር በውስጥም ኾነ በውጪ ተንኳሽ ኀይሎች በሚነካ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነትና በመደጋገፍ የመመከት ታሪክ እንዳለው አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ጊዜም የተጋረጠውን የሕልውና አደጋ ለመመከት ሕዝቡ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ያደረጉት ድጋፍም የዚሁ ታሪክ አካል እንደኾነ  ገልጸዋል።

እንደ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ ምሳሌ መኾን እና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖን መቋቋም የሚቻለው በጋራ ትግል ስለኾነ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የድርሻውን አበርክቶ ሊወጣ እንደሚገባም መልዕክት ማስተላለፋቸውን የአሚኮ ዘገባ አመላክተዋል።