ዩኒየኑ ለውጭ ገበያ ቡና ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

ጥቅምት 1/2015 (ዋልታ) የይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን በ2014 በጀት ዓመት 1 ሺሕ 700 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

ዩኒየኑ 19ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዲላ ከተማ አካሂዷል፡፡

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዮት ደምሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውን የተፈጥሮ ቡና አምራች አርሶአደር ከምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የህብረት ሥራ ማህበራት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባቸው ገልጸዋል ።

ዩኒየኑ ከባንኮች ብድር እንዲያገኝ ዞኑ የ6 መቶ ሚሊዮን ብር ዋስትና መግባቱን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው ዩኒየኑና ማህበራቱ ያሉባቸውን የአሠራር ችግሮች ለይተው በማረም የዓመቱ ዕቅድ ከግብ እንዲደርስ ከባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል ።

የይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ እርቅሁን ወልደጊዮርጊስ ባለፉት ዓመታት የገበያ ትስስር ለመፍጠር አዳዲስ የቡና መዳረሻዎችና ባዛሮች ቡናን እያስተዋወቁ ገዥዎችን ለማፈላለግ ባደረጉት እንቅስቃሴ ጥሩ ውጤት ማስመዝገባቸውን አስታውሰዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት 1 ሺሕ 700 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸው ይህም ከባለፉት ዓመታት የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል ሲል የዘገበው ደሬቴድ ነው፡፡

በቡና አሰባሰብና አዘገጃጀት ለይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱን ጠቁመው ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት በማድረግ ሥራ መጀመራቸውን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል ።

በጉባኤው የዩኒየኑ የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2015 ዓ.ም ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ጸድቋል፡፡