ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ልዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኮሪደር ለማድረግ እየተሰራ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ግንቦት 2/2016 (አዲስ ዋልታ) ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን የሀገሪቱ ልዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኮሪደር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በኢትዮጵያ ችግሮችን በዘላቂነት መሻገር የሚያስችሉ ትክክለኛ የልማት ፖሊሲዎች እየተተገበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ በተጀመሩ ኢኒሼቲቮች ለውጥ መምጣቱንም አንስተዋል።

በተለይ በበጋ መስኖ የስንዴ ልማት ኢትዮጵያን ከልመና የሚያላቅቅና ለአህጉሪቱ ምሳሌ የሆነ አዲስ ታሪክ መጻፉን ነው የተናገሩት።

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም እንደ ሀገር የታቀዱ የልማት ግቦችን ለማሳካት በበጋ መስኖ በተለይም በቋሚ ሰብል ልማት ላይ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

ክልሉ ለመስኖ ልማት የሚውል ሰፊ መሬት እና ትላልቅ ወንዞች ያሉት መሆኑም የመልማት እድሉን እንደሚያሰፋው ጠቅሰዋል።

ይህንን እምቅ አቅም በመጠቀም ክልሉን የአትክልትና ፍራፍሬ የልማት ኮሪደር ለማድረግ ሰፊ ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ክልሉ በሙዝ፣ በአቮካዶ፣ በማንጎ እና በደጋ አፕል ምርቱ እንደሚታወቅ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።

ከሙዝ ልማት ብቻ በሄክታር ከ300 እስከ 400 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ አንስተው የሌሎች ፍራፍሬዎችን ምርታማነት ለማሳደግ ልዩ የኤክስቴንሽን መርኃ ግብር ወጥቶ በመተግበር ላይ ነው ብለዋል።