ዲጂታል ኢኮኖሚው ከ4 ዓመት በኋላ በጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ላይ የ1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ጭማሪ ሊያመጣ እንደሚችል ተገለጸ

ጥቅምት 14/2017 (አዲስ ዋልታ) እ.ኤ.አ. በ2028 የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ በጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ላይ ከ1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ሊያስገኝ እንደሚችል የጂኤስኤምኤ ሪፖርት አመላከተ።
ጂ.ኤስ.ኤም.ኤ የሞባይል ስነ-ምህዳርን አንድ የሚያደርግ አለም አቀፍ ድርጅት ሲሆን Driving Digital Transformation of the Economy in Ethiopia የተባለ ሪፖርት በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱም የቴሌኮም ማሻሻያ እና የሞባይል ቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንቶች በ2028 ከ 1 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ስራዎች እንደሚፈጥሩ ጠቁሟል። ለመንግስትም ተጨማሪ 57 ቢሊዮን ብር ከታክስ ገቢ እንደሚያስገኙ ተገልጿል።
አሁን ላይ የቴሌኮሙ ዘርፍ 700 ቢሊዮን ብር ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) አበርክቶ አለው። የሞባይል ኢንተርኔት ግንኙነቶች 65 በመቶ ማደጋቸውን እና የአራተኛ ትውልድ ኔትወርክ (4ጂ) ሽፋን በስምንት እጥፍ መጨመሩንም ሪፖርቱ ጠቁሟል።
በአጠቃቀም ክፍተት ምክንያት በኔትወርክ ሽፋን ውስጥ ቢኖሩም 76 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የሞባይል ኢንተርኔት አይጠቀምም ። በታለመ የፖሊሲ ማሻሻያ ይህ ክፍተት በ2028 ወደ 66 በመቶ ሊያሽቆለቁል የሚችል መሆኑንም ሪፖርቱ ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ የ90 ሚሊዮን የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች እና የ70 በመቶ የስርጸት ምጣኔ መኖር የሞባይል ገንዘብም የሃገሪቱ የገንዘብ ዝዉውር ስርዓት አካታች እንዲሆን ማድረጉ ተነስቷል።
ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ያለውን የዲጂታላይዜሽን አቅም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም የሚያስችሉ የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችንም ዘርዝሯል።
በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት አቅርቦትን ማስቀደም እና ፈጣን የቴሌኮም ማሻሻያ ማድረግ እንዲሁም የሞባይል ቀፎዎችን ዋጋ ተመጣጣኝነት ማሻሻል፡ ከምክሮቹ መካካል ናቸው ።
የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎቶችን ማስፋፋት እና የዲጂታል ክህሎትን እና የመንግስት አገልግሎቶችን ማሳደግም ጂኤስኤምኤ የዘረዘራቸው ወሳኝ የፖሊሲ ምክሮች ናቸው።