ሚያዝያ 19/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲወለድ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
በተለይ በምርጫ ወቅት ዜጎች በልዩ ልዩ መንገዶች ተሳትፎአቸውን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡት፡፡
ካርድ ወስደው በሰላማዊ መንገድ ለመምረጥ ራስን ከማዘጋጀት በዘለለ፣ በሲቪክ ማኅበራት አማካኝነት የምርጫው ሂደት ግልጽና ተአማኒ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጠቁመዋል፡፡
የሲቪክ ማኅበራት በካርድ አሰጣጡ ዙሪያ፣ የምርጫ ቅስቀሳን በተመለከተ እና የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በቅድመና ድህረ ምርጫ ወቅት የሚያጋጥሙ ግጭቶችን ለማስቀረት ዜጎች የማይተካ ሚና እንዳላቸው መዘንጋት የለበትም ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡